እያበሉ ማሰር፣ እያሰሩ ማብላት
ገመና የሚለው ቃል በኢትዮጵያና ወደ ማሕበራዊነት ያዘነበለ የማሕበረሰብ ባሕል ባላቸው አገሮች እና ሕዝቦች ትልቅ ፋይዳ ያለው ቃል ነው። ብዙ የኑሮ ችግር ውስጥ የሚያልፉና ችግራቸውን በጓዳቸው ለራሳቸው ብቻ ይዘው ማንም ሳይረዳቸውም ሳይርረዳቸውም ከኑሮ ጋር እየታገሉ የሚኖሩ ቤተሰቦች ልቅሶ ቤታቸው ውስጥ ሲከሰት “አጋለጥሽኝ” “አጋለጥከኝ” በማለት የሟችን ስም እየጠሩ ያለቅሳሉ። ምክንያቱም በልቅሶው ዕለት በገዛ ቤታቸው እነርሱ ሐዘንተኛ እንግዳ ሆነው፣ ጓዳቸውን እየበረበሩ ያለውን ቁሳቁስ አገላብጠው ለለቀስተኛ እንግዳ መስተናገጃ ምግብ እና ማረፊያዎችን የማዘጋጀት ኃላፊነት ግን የጎረቤት ይሆናልና ነው። በዚህ ኢትዮጵያዊ የወገን ለወገን መደራረስ ልምምድ ውስጥ ጎረቤቴ የቤቴን ጉድለት እስከ ጥግ ዘልቆ የሚያውቀውና የሚያይበት አንዱ አጋጣሚ የ ሐዘን ጊዜ ነው። ሐዘን፣ ችግር፣ መከራ ገመና ገላጭ ነው። የሰው የድሀነት ጥግ የሚታወቀው ታሞ መታከሚያ፣ ታርዞ መልበሻ፣ ተርቦ መጉረሻ ሲያጣ እና ወደ ልመና ሲገባ ነው። ችግር ገመና ገላጭ እና አጋላጭም ነው። ይህን እንደ መልዕክቴ መግቢያ የተጠቀምኩት የግለሰብን ገመና ሐዘንና ሕመም የመሳሰሉ ድንገተኛ እና አስከፊ ችግሮች እንደሚያጋልጡ ሁሉ የቤተክርስቲያንም ገመና ለእርሷ ከባድ በሆኑ ችግሮች ስትጠቃ ሲገለጥ አይቼ ነው። ያጋለጧት እነማን ናቸው? ቤተክርስቲያን እንዴት ታልቅስ? ቆሻሻዋንና ጉድለቷ ከሐዘኗ በፊት እንዲወገድ ሊያደርጉ ሲችሉ ለምን ዝም ብለው ጠበቁ? ጓዳን በግድ የሚያስከፍተው ቀን የማይደርስ መስሏቸው ይሆን?
በአሁኑ ሰዓት ቤተክርስቲያንን ከከፍታዋ የሚያወርዳትና ከንጽሕናዋ የሚያጎድላት አደባባይ ላይም አውጥቶ ገመናዋን ያ ያሰጣው የግብረሰዶማዊነት ጉዳይ ጓዳዋ በጎረቤቶች እንዲፈተሽ አስገድዷል። በአሁኑ ሰዓት “ለካ እንዲህ ናችሁ እንዴ?” የማይላት (የማይለን) ያለ አይመስለኝም። ብዙ የምንከሰስና የምንወቀስባቸው ጉዳለቶች ቢኖሩንም ይኸኛው ብሷል። ቤተክርስቲያን ከግብረሰዶማውያን የደረሰባት ወረራ በሐዘን ጊዜ የግለሰብ ጓዳ ጉድለት እንደሚገለጥበት ዓይነት የጓዳዋን ገመና ደጅ እንዲስሰጣ አደርጓል። ይሄ ለምን ሆነ? እንዴት እዚህ ደረስን? ይህን ያህል ድህነት እንዴት ሊመታን ቻለ? የሚሉ ጥያቄዎች በብዙዎቻችን ዘንድ መነሳታቸው አይቀርም። ለዚህ የሚስሰጡ ተጨማሪ ምላሾች ሊኖሩ ቢችሉም በእኔ ግምገማ ቀዳምዊ ምክንያት ሆኖ ያገኘሁት የቤተክርስቲያን አገልጋዮች ለእውነት የመቆም አቅም በቤተክርስቲያን ካድሬያዊ “አሠራር” መታሰሩን ነው። እንዳይናገሩ አፋቸውን፣ እንዳይራመዱ እግራቸውን ያሰረ አሰራር በአገልጋዮች አንገት ላይ ገብቷል። እኔ ባለሁበት አገር ፈረንጅ ውሻውን ሲያዝናና በረጅም ገመድ አስሮ እንደሚሄደው የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ሕይወት ለቤተክርስቲያን መስዋዕት አድርገው የሰጡ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች እውነቱን እያወቁ ዝም ያሉት አፋቸውን ያሰረ ካድሬያዊ አሰራር ስላለ ነው።
ሐዋርያው ጳውሎስ “...የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር...” (ዘዳ.25፥4) የሚለውን በተምሳሌነት ተጠቅሞ መንፈሳዊ ትምህርት በመስጠት የሚያገለግሉትን በሚያስፈልጋቸው ቁሳዊ ነገር መደገፍ እንደሚገባ ለማስተማር ጠቅሶታል (1ቆሮ.9፥9፤ 1ጢሞ.5፥18)። ቤተክርስቲያንም ይህንን እውነት ተቀብላ የሚያገለግሉኝን የጸጋ ሥጦታዎች በገንዘብ እና ቁሳቁስ ማገዝ አለብኝ በማለት በደሞዝም በሌላም መንገድ አገልጋዮቿን ስትደግፍ ቆይታለች። ይህም ድጋፍ ለአገልጋዮች እንደ ዕርዳታ የሚሰጥ ሳይሆን እንደ መብት የሚግገባቸው (1ቆሮ.9፥3_18፤ ዕብ.13፥10) መሆኑን ጳውሎስ ቁልጭ አድርጎ አስቀምጦታል። በመሆኑም ሙሉ ጊዜያቸውን በቤተክርስቲያን አገልግሎት ላይ ያዋሉ ወንድሞችና እህቶች አገልግሎታቸውን እንደ ሙያ ቆጥረው ሳይሸማቀቁ ቢገለገሉበት የተገባ ነው። የቤተክርስቲያን አገልጋይነት በራሱ ሞትንም ሊያስከትል የሚችል በነበረበት በስደቱ ዘመን ብዙዎች የማይሻሙበት “የመከሩ ጌታ ለመከሩ ሠራተኞችን እንዲልክ” ብርቱ ጸሎት በሚያስፈልግበት ዘመን ይህ አካሄድ በሰላም ሲሰራበት ቆይቷል። የደርግ መንግሥት መውደቅን ተከትሎ የመጣው አንጻራዊ ነጻነት ቤተክርስቲያን ወደ ጎን እንድትሰፋ ያደረጋት ቢሆንም በዚያው ልክ ወደታች ሥር እንድትሰድ ባለማድረጉ የትምህርት ነፋስ (ኤፌ.4፥14) እየወዘወዘ የጣላት ብዙም ሳይቆይ ነበር። ዛሬ የምንጨቃጨቅበት ሐዋርያና ነብይነት አልለ ወይስ የለም የሚባለውም አጀንዳ የተጠነሰሰው ወይም የተንቀሳቀሰው ያኔ ነበር።
የስደቱ ዘመን የፈጠረው የአገልጋይ እጥረት፣ በ“ነጻነቱ” ዘመን ለተፈጠረው የሕዝብ ብዛት ቤተክርስቲያን ተመጣጣኝ አገልግሎት መስጠት እንዳትችል አድርጓታል። በደርግ ዘመን አብዮቱን በካድሬነት እና በውትድርና ያገለገሉ ሰዎች አንዳንዶቹ በአደባባይ ሌሎቹም በእስር ቤት ጌታን ተቀብለው ስለነበር ከእስር ቤት ወጥተው ቤተክርስቲያንን ሲቀላቀሉ ደርግ የሰጣቸው የካድሬነት ሥልጠና አሠራር ተጠቅመው የቤተክርስቲያንን ላዕላይ አመራር ተቆጣጠሩት። በስደቱ ዘመን የነበረ “የአሠራርን” ቴክኒካዊ ባሕርይ ያልተማረ እንደ እርግብ የዋህ የነበረው አገልጋይ ወደኋላ እየተገፋ የሽማግሌዎቹም የሙሉ ጊዜ አገገልጋዮቹም ጉባኤ በእነዚህ የሰለጠኑ ብልጦች ቁጥጥር ሥር ወደቀ። ቤተክርስቲያንም ሕዋስነቷን (ኦርጋኒዝም) አጥታ ወደ ተቋምነት (ኦርጋናይዜሽን) ተቀየረች። የአገልጋዮች ደሞዝተኛነት በጸጋ ሥጦታቸው ሳይሆን እንደ ደርግ መሥሪያ ቤቶች በትምህርት ደረጃቸው ይከፈላቸው መባል ተጀመረ። የወጣትነት ዕድሚያቸውን በትምህርት ሳይሆን የነፍስ ዋጋ በሚያስከፍለው አገልግሎት ላይ ያሳለፉ አባቶች ወደ ኋላ እየተደረጉ በብልጠትና በአሰራር የሰለጠነ አዕምሮ ያላቸው የቀድሞ ካድሬዎችና የአሁን “ወንድሞች” ፊት ለፊት መውጣት ጀመሩ። ያኔ ነበር ቤተክርስቲያን የቁልቁለት ጉዞዋን የጀመረችው። ብዙዎች እኔ ተቀጥሬ ሳይሆን ተጠርቼ በጥሪ የማገለግል ነኝ ብለው ሲከራከሩ፣ አይደለም እኛ የቤተክርስቲያን ሽማግሌዎች ቀጥረንህ ነው የሚሉ ሙግቶች የከተማው መነጋገሪያ የነበሩበት ዘመን ትዝ ይለኛል። እነዚህ ካድሪያዊ አገልግሎትን መርህ የተከተሉ የትናንት ካድሬ የዛሬ ሽማግሌዎች እንደምንም ብለው ጥሪን ሳይሆን ቅጥርን እንደ ቤተክርስቲያን አሠራር እዲሰፍን ካደረጉ በኋላ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮችን በሚከፍሏቸው የወር ደሞዝ (ያኔ ቀለብ ነበር የሚባለው) አፋቸውን አስረው “እኛ የምንልህን ካልሰማህ እናባርርሃለን!” ማለት ጀመሩ። በካድሬነት ዘመናቸው የሰለጠኑበት ውስጣዊ አሰራር ስላላቸው እንዴት ማባረር እንደሚቻል ለማወቅ ለነርሱ ቀላል ነበር። እግዚአብሔርን ስለማያውቁም፣ ስለማይፈሩም ብዙ ዋጋ ከፍለው በአስቸጋሪው ዘመን ቤተክርስቲያንን ያገለገሉ ሰዎችን በቀላሉ በአሰራር አባርረዋል፣ በማባረርም ላይ ይገኛሉ። ለእነርሱ መለኪያ ካድሪያዊ አሰራር እንጂ መለኮታዊው ጥሪ ወይም ሕያው ቃሉ አይደለም። አፉን አትሰር የሚለውን የታዘዙ መስለው ደሞዝ ቢከፍሏቸውም ደሞዝ መክፈልን እንዴት አድርገው አፍ ማሰሪያ እንዳደረጉት ለብዙዎች ግልጽ የሆነው በጣም ቆይቶ ነው። ከአገልግሎት ሰዎችን ማባረርን ማስፈራሪያ ያደረጉት “እኛን ካልሰማህ፣ የእኛን ጥቅም ካላስጠበቅህ እናባርርሃለን፣ አርፈህ ዳቦህን ብትበላ አይሻልህም?” ከተባሉ እና በዳቦ ማስፈራራት ከደረሰባቸው ሰዎች አንዱ በመሆኔ ይህን ስናገር አልፌበት ጭምር መሆኑን ለመግለጥ እወዳለሁ። እሺ ጌታዬ! እያሉ ለሽማግሌዎች፣ ለኮሚቴዎች፣ ብቻ አመራሩን ለተቆጣጠሩት መስገድ ዳቦ ሳያጡ ለመኖር ወሳኝ ከሆነ ሦስት አሥርት ዓመታት አለፉ። ይሄ ባጭሩ ያጋራኋችሁ ግምገማ ሰፊ ትንታኔና በምስክርነቶች የታጀበ ጥናታዊ ጽሑፍ ሊሰራበት የሚገባ ርዕሰ ጉዳይ ነውና እኔ እዚሁ ላይ ባጭሩ ትቼው ሰፊውን ሥራ ለወደፊት የምርምር ጥናት አድራጊ ልተወውና ወደ መፍትሔ አቅጣጫው ልመለስ።
ቤተክርስቲያን በዚህ መንታ መንገድ ላይ ባለችበት ባሁኑ ወቅት ምን ማድረግ አለብን የሚለውን ከመናገሬ በፊት ከዚህ በፊት በተናጠል የተወሰዱትን እርምጃዎች ባጭሩ ልጠቁም። ዛሬ የምናያቸው በሐዋርያና በነቢይ የሚመሩ “ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማሕበር” የሚመስሉ ቤተክርስቲያናት የተወለዱበት አንዱና ዋናው ምክንያት ከላይ የጠቆምኩት በካድሪያዊ አሠራር የተደራጁ የቤተክርስቲያን መሪዎች በጥሪ የመጡ አገልጋዮችን አላሰራም ስላሉ እንደሆነ አውቃለሁ። ቤተክርስቲያን በባለ ራዕይ እንጂ በኮሚቴ ልትመራ አይገባም ብለው መንፈሳዊ አብዮት ያስነሱ ሰዎች ችግርን የፈቱት በሌላ ችግር ሆነ። አምባገነንና ሥጋዊ የሆነውን የካድሬ ቡድን ጥሪ አለኝ በሚል ነገር ግን የቤተክርስቲያንን አመራር በማይርረዳ አምባገነን ሐዋርያ/ነብይ ብሎ ራሱን በሚጠራ ግለሰብ ተኩት። ችግርን በችግር መፍታት ማለት ይህ ነው። ለጊዜው ከካድሪያዊ አሰራር ነጻ በመውጣታቸው ምክንያት የነጻነት አየር የተነፈሱት የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች የቤተክርስቲያንን ሐብት የሚያስተዳድሩበት አቅም አልነበራቸውም። ሌሎች ባለሙያዎች እንዳያግዟቸው ደግሞ በካድሬዎቹ ከደረሰባቸው ‘ትራውማ’ ገና አላገገሙም። በዚህ ‘ፎቢያ’ ውስጥ ሆነው በመሰላቸው ሲመሩ በምቾት እና ሙስና አሰራር ውስጥ ገብተው እነርሱም በተራቸው ሌላ አሰራር ፈጥረው ውኃ፣ ዘይት... እስከመሸጥና የቤተክርስቲያንን ተቋማዊነት አንድ ደረጃ አሻሽለው የንግድ ድርጅት አድርገዋት ቁጭ አሉ። በጥቅም ተይዘው እውነትን በነጻነት እንዳይናገሩ አፋቸውን የተለጎመባቸው፣ ይህንን ልጓም አውልቀው በነጻነት ይናገሩ ዘንድ አፋቸውን ከካድሬያዊ አሰራር እስራት ሲያስለቅቁ የስህተት ትምህርትን እና አሰራርን ይናገር ዘንድ የተፈታ አፍ ባለቤቶች ሆነው ተገኙ። ያኔ በገንዘብ ማስፈራራት አፋቸው ታሰረ፣ አሁን ደግሞ በተፈታው አፋቸው የስህተት አሰራርና ትምህርትን ለቀቁበት። እነርሱም በተራቸው የሚቃወማቸውን የሚያባርሩበት ፕሬዝዳንታዊ፣ ባለራዕይ የሚባል አሰራር ፈጥረው የሚመሩትን ምዕመን “አንተ የኔ ራዕይ አስፈጻሚ ነህ” ብለው እንዳይናገር አፍነውት ቁጭ አሉ። ለዚህም ነው እኛ ልጆች ሆነን “በእኔ ጉሮሮ አጥንት ይቀርቀር፣ በኔታ ጉሮሮ ጠጅ ይንቆርቆር” በማለት ፊደል ያስቆጠሩንን እንደምናሞግስ እነርሱን የሚያመልክ ምዕመን ያላቸው በአጃቢ የሚንቀሳቀሱ እስከመሆን የደረሱት። አሁንም የእነዚህ የግለሰብ ራዕይ ለማስፈጸም ተቋቁመናል የሚሉትን ቤተእምነቶች ጉዳይ መርምሮ ሰፋ ያለ ጥናታዊ ጽሑፍ ለትምህርትም ለታሪክም ለሚያዘጋጅ ሰው ልተወውና ወደ አሁናዊ መፍትሔ መለስ ልበል።
ቤተክርስቲያን አሁን ላለችበት ምስቅልቅል ከዳረጋት ነገር መውጫ ሊሆናት ስለሚቻልባቸው አማራጭ መፍትሔዎች ማሰብም መጸለይም ከጀመርኩ ሰንበት ብያለሁ። በመጠኑም ቢሆን የመከራውንም ጊዜ ሆነ ያሁኑን ዘመን ችግር ለማየትም ለመገምገምም ሞክሪያለሁ። አሁን ቤተክርስቲያን ያለችበት ሁኔታም እጅግ አደገኛና አስጊ እንደሆነም እገነዘባለሁ። ከሁሉም በላይ ደግሞ ይህ ግምገማ የእኔ ብቻ እና በፆም በጸሎት የሚደረስበት ውስብስብ ሳይሆን የመውለጃዋ ወር እንደገባ ሴት ሆድ ፍጥጥ ብሎ የሚታይ እውነት እንደሆነና ለብዙዎች የተገለጠ መሆኑንም እገነዘባለሁ። የችግሩ ሥርና መሠረትም ከቤተክርስቲያን አወቃቀር እና አመራር ጋር እንደተያያዘ ተመልክቻለሁ። የአመራርና አወቃቀር ሁኔታ ሳይስተካከልም ይሄ ከአናቱ የጀመረው ችግር ወገቡን ወይም ሸኮናውን ተመትቶ ሊወገድ እንደማይችል አፍሪካን የሚያውቅና አፍሪካዊ የሆነ በደንብ እንደሚገባው እገምታለሁ። እንዲህም ስለማስብ ነው የተሻለው እና ፈጣን መፍትሔ በቀዳሚነት “priesthood of all believers” በሚለው ተሐድሷዊ መርህ ምዕመኑን ማንቃት ላይ በተከታይነት ደግሞ በደሞዝ ምክንያት አፋቸው የተለጎመውን የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ችግርም መፍታት አስፈላጊ ነው የምለው።
1. የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ከፊል ጊዜ አገልጋዮችና ምዕመናን የቤተክርስቲያን ተስፋዎች ናቸው
ሙሉ ጊዜን ለቤተክርስቲያን ለአገልግሎት መስጠት ለአገልግሎት ጥሪ ምላሽ መስጫ ብቸኛ መንገድ ተደርጎ ሲታሰብ ቆይቷል። ይሄ አካሄድ በየዋህነት ስንከተለው የነበረ እንጂ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ብቸኛ አማራጭ ይሄው ብቻ ሆኖ አይደለም። ቀደም ባሉት ጊዚያት ሌሎች አማራጮችት ተገምግመው የሚኬድበት ሌላ መንገድ እንዳልለ አይታሰብም ነበር። ለዚህ ማሳያው ሥራውን ትቶ ሙሉ ጊዜውን ካልሰጠና ስሙ የቤተክርስቲያን ሰራተኞች ደሞዝ መክፈያ ፔሮል ላይ ካልሰፈረ አንሾምም የሚለው የቤተክርስቲያን ካድሪያዊ አሰራር ምስክር ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ሐዋርያ ሆኖ ቀን ሙሉ ጊዜውን ማታ ደግሞ የድንኳን ሥራውን እየሰራ የከፊልም የሙሉም ጊዜ አገልጋይ በሚባል መልክ ሲያገለግል ሹመትም አልቀረም፣ ሥራም አልተከለከለም ነበር። ታዲያ ቤተክርስቲያናት ለምን የከፊል ጊዜ አገልጋዮችን አይሾሙም? ብዙዎች በግልጥ የሚሰጡት ምላሽ “የማንከፍለውን ሰው ልንቆጣጠረው አንችልም” የሚል ነው። ስለዚህ የቤተክርስቲያንን ቁሳዊና ሰባዊ ሀብት መቆጣጠርን መሠረት ያደረገ አሰራር እስካለ ድረስ ችግሩ ይቀጥላል። የቤተክርስቲያን አገልግሎት ደቀመዝሙር ማድረግ እንጂ “ቁጥጥር” እንዳልሆነ የተረዳ አደረጃጀትና አሰራር በአስቸኳይ ካልተቀየሰ ፍሬን በጥሳ ወደ ገደል እየሮጠች ያለችውን ቤተክርስቲያን ከመገልበጥ፣ ከመበረዝ፣ ከመጥፋት መታደግ አይቻልም። ግብረሰዶምን የሚያክል ጉድ ለማስተናገድ ከመዳዳት የባሰ ፍሬን መበጠስ ሊያጋጥማት ይችላል ብዬ ስለማልገምት ነው “ፍሬን በጥሳለች” ወደ ገደል እየተቃረበች ነው የምለው። ስለዚህ የወደፊቷን / የነገዋን ቤተክርስቲያን ለመገንባት የምትሹ ሁሉ ትኰረታችሁን የከፊል ጊዜ አገልጋዮችን ማብዛትና ማስታጠቅ ላይ ብታደርጉ ለእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን ትልቅ ውለታ ትውላላችሁ። በአሁኑ ጊዜ አፋቸው ተዘግቶ መናገር ያልቻሉ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ባሉባት ቤተክርስቲያን ውስጥ በብቸኝነት በሕይወት መኖራቸው የተረጋገጠና ስለ ግብረሰዶም አደጋ መተንፈስ የቻሉት እነዚህ የከፊል ጊዜ አገልጋዮች መሆናቸው የሚዲያ አደባባዮችና የቤተክርስቲያን ምስባኮች ይመሰክራሉ። የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች የካድሬያዊ አሰራር ሰለባዎች ሆነው በእግዚአብሔር ጉባኤ ፊት ቆመው መጽሐፍ ቅዱሳቸውን የሚሰብኩ ሳይሆኑ ካድሬያዊው አሰራር ያመነጨውንና በእነርሱ የተሰጣቸውን ደብዳቤ የሚያነቡ ሆነዋል። የእውነትን እስትንፋስ እስካሁን በብቸኝነት የሚተነፍሱትን የከፊል ጊዜ አገልጋዮች በእነዚህ ደብዳቤዎች እየተወገዙና እየተባረሩ መሆናቸው የአደባባይ ምስጢር ነው። የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ደቀመዝሙር ማፍራትም፣ ለእውነት ጠበቃ መቆምም አልቻሉም። አሁን ያሉበት አጣብቂኝ በካድሬያዊ አሰራር ተጠልፈው ተመትራ በተሰጠቻቸው ቦታ ላይ ቆመው ተጽፎ የተሰጣቸውን ቤተክርስቲያንና ውደ የከፊል ጊዜ አገልጋዮቿን የሚገድል ደብዳቤ ማንበብ ሆኗል። እነዚህ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች በእውቀትም፣ በጥሪም፣ በዝግጅትም አንሰው ሳይሆን እውነትን መናገር ያልቻሉት አፋቸው ካድሬያዊው አሰራር በሚከፍላቸው ደሞዝ ተሸብቦ ነው ዝም ያሉት። ይህን ልጓም አውልቀው በተናገሩ ቅጽበት ከአገልግሎትም ከፔሮልም ይሰረዛሉ። ይህን ዋጋ መክፈል ከባድ እንደሆነም ይገባኛል። አማራጫቸው ጠባብ እንደሆነ እርረዳለሁ። አልፈርድባቸውም፤ ድካማቸውንም ከመናገር አልረፍቅም። የከፊል ጊዜ አገልጋዮችን አገልግሎት ማነቃቃት፣ ማደራጀትና ማስታጠቅ ለቤተክርስቲያን ሕልውና ወሳኝ መሰረት ነውና ይህ መፍትሔ የእነርሱም መዳኛ ይሆናል። የከፊል ጊዜ አገልግሎትንና አገልጋዮችን እንዴት እናንቃ? አስተያየቶቻችሁን ለግሱ።
2. የሙሉ ጊዜ አገልጋዮችን አፍ የለጎመውን የደሞዝ ልጓም ጉዳይ መፍታት ዘላቂ መፍትሔ ነው
በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ያሉ አብያተክርስቲያናት ውስጥ ስንት የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች እንዳሉ አላውቅም። አንድ ተማሪ ብዛታቸውንና ተጽዕኖ ፈጣሪነታቸውን የሚያነጻጽር የመመረቂያ ወረቀት ቢሰራበት መልካም ይሆናል። ይህን ቁጥር መጥቀስ የፈለኩት እነዚህን የሚያህሉ የተጠሩ እና የቤተክርስቲያን ጉዳይ ዕለት ዕለት በልባቸው የከበደ (2ቆሮ.11፥28) አገልጋዮች በአንድ ድምጽ በያሉበት ቢጮሁ ኢያሪኮ እንደፈረሰ የግብረሰዶማውያን ዕቅድ ሊፈርስ እንደሚችል ቅንጣት ያህል አልጠራጠርም። የሙሉ ጊዜ አገልጋዮቻችን የዚህ ርኩሰት ተቃዋሚዎች እንጂ ደጋፊዎች እንደሆኑም አላስብም። እዚህ ላይ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ስል በካድሪያዊ አሰራር ተጠልፈውና የሥርዓቱ ጥቅም ተጋሪ የሆኑትን ቀንሼ መሆኑ ይታወቅ። በቁጥር ጥቂት ሆነው ለቁሳዊ ጥቅማቸው ያደሩ የሙሉ ጊዜም ሆነ የከፊል ጊዜ አገልጋዮች እንዳሉ የተረዳሁ መሆኔን በዚህ አጋጣሚ መጠቆም እወዳለሁ።
የሚያበራየውን በሬ አፉን ማሰር የሚለው አባባል በመጽሐፍ ቅዱስ የታየው እየሰራ/እያገለገለ ያለውን አገልጋይ ቀለብ አትከልክለው ለማለት እንደተጠቀሰ እናውቃለን። ይህ አፍ የማሰር ካድሪያዊ ‘አገልግሎት’ በአሁኗ ቤ/ክ ካድሬያዊ አሰራር ውስጥ እየተተገበረ ያለው በሁለተኛው የ “አፉን አትሰር” መንገድ ነው። የመጀመሪያው የማሰረ መንገድ አገልጋዮች ስላገለገሉ ገንዘብ ሊከፈላቸው አይገባም፤ በነጻ የተቀበሉትን በነጻ ይስጡ (ማቴ.10፥8)፣ ወዘተ... ከሚለው በመነሳት ነው። ሁለተኛው አፍ ማሰር ደግሞ አገልጋዮች የተጠሩበትንና የገባቸውን እውነት ዋጋ ከፍለው በድፍረት እንዳይናገሩ አፋቸውን በማስፈራራት በማሰር ካድሬያዊውን አሰራር ለማገልገል ብቻ አፋቸው እንዲከፈት የሚያደርገው ነው። ይህም በገንዘብ የምደግፍህ/ ደሞዝ የምከፍልህ/ ቀለብ የምሰፍርልሕ... እኔ ያመንኩበትን ብቻ ስትናገር ነው የሚል ነው። አፍህ የማይታሰረው የእኔ አፈቀላጤ ስትሆን ነው። እኔ የማምንበትን፣ በካድሬያዊ አሰራሬና ጉባኤዬ የወሰንኩትን ስታነብ አፍህ ይፍፈታል። የእግዚአብሔርን ቃል ስትናገር ግን ደሞዝ በመከልከል አፍህን የሚያኝከው በማሳጣት አስረዋለሁ ማለት ነው። ለመንፈሳዊ አገልጋይ ደሞዝ አይገባውም ብሎ መከልከልና ፣ የካድሬያዊ እና ባለ ራዕይን ፈቃድ ብቻ ካልተናገርክ አስረዋለሁ ብሎ የአገልጋዮችን አንደበት ማሰር በዚህ ሁኔታ ስለሚለያዩ ነው ሁለት ዓይነት ማሰር እንዳልለ ለማሳየት የሞከርኩት። ቤተክርስቲያን በግብረሰዶም አጀንዳ ስትታመስ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ዝም ማለታቸው በሁለተኛው አሰራር አፋቸው መታሰሩን ያረጋግጥልናል። በመጀመሪያውም ሆነ በሁለተኛው መንገድ የታሰረውን የሙሉ ጊዜ አገልጋዮችን አፍ ለማስፈታት አስተምህሯዊም ተግባራዊም እንቅስቃሴ መጀመር ለወደፊቷ ቤተክርስቲያን ቀጣይነት ውሳኝ ጉዳይ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።
የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ራሳቸውን የሚችሉባቸው ልዩ ልዩ የማበረታቻ ፕሮጀክቶች መንቀሳቀስ መቻል አለባቸው። ልጆቻቸውንና የትዳር ጓደኞቻቸውን ለከፋ ችግር የሚጥል የእስራት እና የማስፈራራት አገልግሎት ዘመን እንዲያበቃ በመስኩ ሙያ ያላችሁ ወገኖች ሁሉ ሙሉ በሙሉ ካልተቆጣጠርንህ አንሾምህም የሚለውን አስተምህሮ መሞገት ቢጀመር መልካም ይሆናል። ይህ አካሄድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ ሳይሆን ልማዳዊ አሰራር መሆኑን እና የግድ ካልሆነ ተብሎ ብዙ ሥራቸውን እየሰሩ ሊያገለግሉ የሚችሉ ጥሪ ያላቸውን ሰዎች ያመከነ አካሄድ መሆኑን መግለጥ ያስፈልጋል። በተጨማሪም ቀድሞውኑ በዚህ አገልግሎት ውስጥ ገብተው መናገር እየፈለጉ አንደበታቸውን ካድሪያዊው አሰራር ያሰረባቸውን የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች በልዩ ልዩ መንገድ ድጋፍ የሚያገኙበትን መንገድ መፈለግ ወሳኝ መሆኑን አውቀን እንድናግዛቸው ለቤተክርስቲያን የሚቀኑትን ሁሉ እጋብዛለሁ። በተጨማሪም አሸናፊው የካድሪያዊው አሰራር ይሆናል ብለው በዚያ መስመር የተሰለፉትንም ፊት ለፊት መሞገት የእንቅስቃሴው አንድ አካል ተደርጎ እንዲታይ ጥሪ አቀርባለሁ። በአሁኑ ጊዜ የተለያዩ የቤተክርስቲያን መድረኮችን የተቆጣጠሩና ታዋቂ ሰባኪያንም በሚቆሙበት መድረክ ላይ ይህን በቤተክርስቲያን ላይ ከሰዶማውያን የተቃጣብንን ሥጋትለመመከት፣ ለመግለጥና ለማጋለጥ ያልቻሉት የመድረክ ገበያቸው እንዳይዘጋባቸው ብለው እንደሆነ መገመት አያዳግትም። ብዙ ሌሎች ጉዳዮችን በትኩሱ እያነሱ ሲጎርሱና ሲያጎርሱ የምናውቃቸው ሰባኪያን ቤተክርስቲያን በእንዲህ ዓይነት የክፉ ቀኗ መድረኳ ላይ ቆመው ሳይናገሩላት መውረድ ያስቻላቸውን ስንፍና ሳልቃወም አላልፍም። አሁንም አልረፈደምና ይህን ክፉ በቤተክርስቲያን ሕልውና ላይ በአሰራርም ሆነ በአስተምህሮ መልክ የመጣውን አደጋ በመቃወም እንዲገለጡ፣ ለምዕመናን እና የከፊል ጊዜ አገልጋዮች ጭምር አቅጣጫ የሚሰጥ መልዕክቶችን ማስተላለፍ እንዲጀምሩ ጥሪዬን አቀርባለሁ። ይህ ሳይሆን ቀርቶ አፋቸውን በገንዘብ፣ በፍርሃት፣ እና በተራ ታዋቂነትን ሸመታ ተጠልፈው ቢቀሩ ታሪክ እንደሚፋረዳቸውና መዳን ለቤተክርስቲያን ከሌላ ሥፍራ ሊሆን እንደሚችል እንዲያውቁትም ከወዲሁ እጠቁማለሁ። ባለመክፈል እያስራቡ አፉን ማሰርም ሆነ፣ በመክፈል እያስፈራሩ የሚናገርበትን አፍ ማሰር ለጊዜው አዋጭ የመሰላቸው የካድሪያዊው ሥርዓት ጠበቆች የእረኞች አለቃ በሚገለጥበት ጊዜ ዋጋችሁን እንደሥራችሁ እንደሚሰጥ እንዳትረሱት ለማሳሰብ እወዳለሁ። የተሐድሶ ጥሪ የደረሳችሁ ወንድሞችና እህቶች በተደራጀ መንገድ መጭውን ትውልድ ልታገለግል የምትችለዋን ቤተክርስቲያን በኃላፊነትና በብልሃት ለመገንባት በተቀናጀ አካሄድ እንነሳ። ይህ ተልዕኮ እንዴት ይቀናጅ የሚለው ላይ ሀሳብ ማቅረብ ይቻላል። በገዛ ደሙ የዋጃት ቤተክርስቲያን በቅሬታዎች አገልግሎት ቀጥላ ድልን ትቀዳጃለች።
